የዋና ዳይሬክተሩ መልዕክት

ሰላም ለሁላችሁም

General Director Of AASTAአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጲያና የአፍሪካ መዲና የሆነች በዓለምም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ከተሞች አንዷ ነች፡፡  ከተማችን ሁሉንም ዓይነት ማህበረሰብ ያቀፈች፣ ለሃገራችን ስልጣኔም ፈር ቀዳጅ ሚናን የምታበረክት፣ በአጠቃላይ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ መስኮች ለማሳከት ለምናስበው የብልጽግና ጉዞ የላቀ ድርሻ ያላት መሆኗ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ በከተማው አስተዳደሩ በተሰጠው ተልእኮ መሰረት በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ማለትም የኔትወርክ መሰረተ ልማት ዝርጋታን በማከናወንና እና የተለያዩ ሲስተሞችን በማበልጸግ እንዲሁም የሳይንሳዊ ምርምርና ፈጠራ ስራዎችን በማከናወን የከተማ አስተዳደሩን ሁለንተናዊ አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

እስካሁን በደረስንበት ደረጃም ከኔትወርክ መሰረተ ልማት እና ተያያዥ ቴክኖሎጂዎች ትግበራ አኳያ ለ112 ወረዳዎች፣ ለ8 ክ/ከተሞች አዳዲስ ህንጻዎች፣ ለትራፊክ ጽ/ቤት ህንጻ፣ ለቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ ለፖሊስ ኮሚሽን፣ ለት/ት ቢሮ የስኩል ኔት ፕሮጀክት፣ ለፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ፣ ለከንቲባ ጽ/ቤትና  ለሌሎችም የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ተቋማት ውጤታማ ስራ ሰርቷል፡፡

በሌላ መልክ ደግሞ ከሲስተም ልማት አኳያ የኢአርፒ ሲስተም፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ስራ እድል ፈጠራ መረጃ ሲስተም፣ የዲጂታል መታወቂያ ሲስተም፣ የኢሰርቪስ ትግበራ፣ የተለያዩ ድረገጾችን ማልማት እና መሰል የሲስተም ልማቶች ተከናውነዋል፡፡ በተጨማሪም የተማከለ የዳታ ሴንተር እና የዳታ አገልግሎት የመስጠት፣ ዘርፈ ብዙ የባለሙያ አቅም ግንባታ ስራ የማከናወን፣ የማህበረሰብ የኢኮቴ ማእከላትን የማደራጀት እና ወደ ስራ የማስገባት ስራዎች ተፈጽመዋል፡፡

በአጠቃላይ ኤጀንሲያችን በርካታ ስራዎችን የሰራ ቢሆንም ከሚጠበቅበት ሚና አኳያ የሚቀሩን ተግባራት በመኖራቸው በአሁኑ ወቅት በልዩ ትኩረት በተቀናጀ ሁኔታ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ ከምንም ጊዜ በላይ የአመራሮች፣ የባለሙያና የባለድርሻ አካላት ቅንጅት የሚያስፈልገን ጊዜ ላይ በመሆናችን ለሃገራችንና ለከተማችን የለውጥ ጉዞ በሙሉ ተነሳሽነትና አቅም የምንቀሳቀስ ይሆናል፡፡

አብርሃም ሰርሞሎ ኪዳኔ

ዋና ዳይሬክተር